null Legal and Justice Affairs standing committee calls for ever greater effort for women substantially involve in leadership.

የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቀሚነት ከማረጋገጥ እንዲሁም ወደ አመራርነት ከማምጣት አኳያ በቀጣይ ይበልጥ ሊሰራበት እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ቁጥጥር በሚያደርግባቸው አስፈፃሚ መ/ቤቶች ከሚገኙ ሴት አመራሮች ጋር የጋራ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡

የውይይቱ ዓላማም ቋሚ ኮሚቴው በሚከታተላቸው የፍትሕ ተቋማት ውስጥ የባለ ብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ማለትም ሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ፍትሀዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግና ምቹ የስራ አካባቢ የተፈጠረላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ መሆኑን ኮሚቴው ገልጿል፡፡

ሴቶች የራሳቸውን መብት ለማስከበርና የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ገፍቶ መሄድ እንዳለባቸውና ከፖሊሲ አኳያም ታይቶ ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዸጥሮስ ወለደሰንበት አስታውቀዋል፡፡

የሴቶችን እኩልነትን ከማረጋገጥ፣ በተለያዩ ምክንያቶች በማረሚያ ቤት ከሚገኙ እናቶች ጋር ያሉና ለትምህርት የደረሱ ሕፃናቶች ጉዳይ እንዲሁም በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራትና ማሻሻል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡