null Legal and justice affairs standing committee noted that…

የኢፌዲሪ የፍትህና የህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስትቲዩት የአሰራር ክፍተቶችን ለመለየት የተጀመሩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንስቲትዩትን የ2010 በጀት ዓመት የ9 ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በህግ ስርአቱ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለማሻሻልና ለፍትህ ዘርፉ ስኬት በሚደረገው ጥናት ዙርያ ባለድርሻ አካላት ጥናቱን እንዲተቹና ሃሳብ እንዲሰጡ መድረክ በማመቻቸት እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

የኢንስቲዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን አበበ እንደገለጹት ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የእለት ተእለት ችግሮችን ከመፍታት አንጻር ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ከስልጣናቸውና ከአገልግሎት አሰጣጣቸው አንጻር በጥናት ለመደገፍ እየተጠና እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

አክለውም ለአካል ጉዳተኞችና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽነትን ለማሳካት ምቹ የስልጠና ዘዴዎች እየተመቻቹ መሆናቸውን ጠቁመው በሰበር ውሳኔዎች ላይ ስለሚታዩ ክፍተቶች ጥናት ማድረግና ለፍትህ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት በቀጣይ አጠናክረው እንደሚሰሩ በቋሚ ኮሚቴው ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ አመልክተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ኢንስቲትዩቱ የአሰራር ክፍተቶችን ለይቶ ማስተካከያ ማድረጉና የተጀመሩት የጥናትና ምርምር ስራዎች አቻ ለአቻ ግምገማ ቀርቦ መገምገሙን እንዲሁም እቅዱ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር የመረጃ ነጻነትና ተደራሽነትን ከማሳደግ አኳያ የሚሰሩ ተግባራትን ያካተተ መሆኑን በጥንካሬ ተመልክቶታል፡፡

የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት በበኩላቸው ከፍታብሄር ህጉ ጋር ተያይዞ የተጀመሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ተፈትሸው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ፣ የፍትህ አካላት አፈጻጸም መለኪያዎችን በሚመለከት ከስራው ጋር በቀጥታ ከሚገናኙ ባለድርሻ አካላት ምላሽና አስተያየት እንዲሰጡ ክትትሉን ማጠናከር እንደሚገባና የፍትህ ስራዎችን በሚመለከት መረጃዎችን የማደራጀት ስራ ትኩረት ተሰጥቶት መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡