null Ministry of farming and natural resource says it is heeding to bring transformation in the sector.

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ምርትና ምርታማነት በሚጨምሩና በዘርፉ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው ምክር ቤቱ ባካሄደው 18ኛ መደበኛ ስብሰባ ነው፡፡ ምክር ቤቱም የ1ኛ ልዩ፣ የ1ኛ አስቸኳይ እና የ17ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤዎችን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡

በመቀጠልም የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርን የ8 ወር የዕቅድ አፈጻፀም ሪፖርትን አዳምጧል፡፡

በሪፖርቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምርትና ምርታማነት በሚጨምሩና ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራና የለውጥ ሰራዊት ግንባታ በማጠናከር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት በየደረጃው ተናባቢ የሆነ አደረጃጀት በመፍጠር የተሻለ የሎጅስቲክ  ስርአት በመዘርጋትና በማሻሻል፣ የሰው ሀይል ሁለንተናዊ አቅምን በመገንባት የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከል በመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢያሱ አብርሃም ገልጸዋል፡፡

የመነሻ ዘር አቅርቦት ሁኔታን በማጠናከርና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የተመሰከረለት ዘር ማምረት፣ የግል ባለሀብቶች ተሳትፎና ዕውቀት ማጎልበት፣ ለዘር ማምረት ሂደት የፍይናንስ አቅርቦት ስርአቱን ማሻሻል ከፌደራል እስከ ክልል ባሉ መዋቅሮች ትኩረት ተሰጥቶአቸው  በከፍተኛ ርብርብ እየተከናወኑ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አልማዝ መሰለ ከቁልፍ ተግባራት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ፈጻሚ አካላትን የማዘጋጀት፣ በዕቅዱ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠርና ሁሉም በየደረጃው ያለው አካል በግብርናው ዘርፍ የየድርሻውን እንዲወስድ ከማድረግ አኳያ በዝግጅት ምዕራፍ የተሰሩ ስራዎች፣ የልማት ሰራዊት ግንባታ፣ የአርብቶ እና አርሶ አደሩን  የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ፍላጎት የማሳደግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት መከናወኑ፣ በህዝብ ንቅናቄ የሚሰሩ የተፋሰስ ስራዎች ላይ የህዝቡን ተሳትፎ ከማረጋገጥ አኳያ የተሰሩ ስራዎችን  በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

አበይት ተግባራትን በሚመለከት የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት የተደረገው ርብርብ ትርጉም ያለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የግብርና መካናይዜሽንን በሚመለከት ከውጭ የሚገቡ የግብርና መሳሪያዎች ላይ ከቀረጥ ነጻ አገልግሎት እንዲፈቀድ መደረጉን፣ የልማታዊ ሴፍቲኔት፣ የተለያዩ የአሰራር ማንዋሎችን ለማዘጋጀት የተደረገው ጥረትም የዕቅዱ ጠንካራ አፈጻፀሞች መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል የሰራዊት ግንባታ ከአደረጃጀት ያለፈና በምርትና ምርታማነት ላይ ውጤት የሚያመጣ መሆን እንዳለበት፣ የአርሶ አደሩን እርካታ በሚመለከት ያልተፈቱ የውስጥና የውጭ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በአግባቡና በወቅቱ ሊፈቱ እንደሚገባ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ ግብአቶችን ተደራሽ የማድረግ ጉዳይና የግብርና መካናይዜሽን ከተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ጋር መተግበር ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የግብርና ቴክኖሎጂዎች በሚመለከት፣ የምጥን ማዳበሪያ ፋብሪካዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን በሚመለከት ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ላይ፣ የኪራይ ሰብሳቢነትን መግታት፣ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት እና የተባይና አረም ቁጥጥር ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ከምክር ቤቱ በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፤ ለጥያቀዎቹ ክቡር ሚንስትሩና የስራ ባልደረቦቻቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ጥያቄዎቹም ተገቢና ለቀጣይ ስራ ጠቃሚና ግብአት የሚሆኑ መሆኑን ሚንስትሩ ገልጸዋል፡፡