null Official: Ethiopian higher education quality and relevance agency to improve its structure.

የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው 23ኛ መደበኛ ስብሰባው የትምህርት ሚኒስቴርን የ2010 በጀት ዓመት የ9 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ገምግሟል፡፡

ሪፖርቱን ያቀረቡት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በየዘርፉ ከተከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል በተለይም እጅግ ወሳኝ ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ሶስት ግቦች ላይ ስለተሰራው ስራ በስፋት ለምክር ቤቱ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

በአጠቃላይ ትምህርት ሁሉም ተማሪዎች በሁሉም አካባቢዎች እና በሁሉም ሃገር አቀፍ የትምህርት ምዘና በሚሰጥባቸው የትምህርት ዓይነቶች ከአንደኛው የትምህርት ክፍል ወደሚቀጥለው ሲሸጋገሩ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት እንዲያስመዘግቡ፡ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በአጫጭርም ይሁን በረጅም ጊዜ የሚሰጡ ስልጠናዎች በምዘና ያጠናቀቁ ሰልጣኞች 90 በመቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ወደስራ ገበያ እንዲቀላቀሉ ወይም ስራ እንዲፈጥሩ እና በከፍተኛ ትምህርት የትምህርት ጥራትንና አግባብነትን በማጎልበት 80 በመቶ የመጀመሪያ ዲግሪ የመደበኛ ተመራቂዎች በተመረቁ በዓመታቸው የስራ ገበያ እንዲቀላቀሉ ወይም ስራ እንዲፈጥሩ ግብ ተይዞ እየተሰራ ስለመሆነ መያዙን ነው የተብራራው፡፡

ግቡም እንዲሳካ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጀምሮ በየክልሉና በየተቋማቱ አስፈላጊ አደረጃጀቶች ተዘርግተውና የማስፈፀሚያ ዕቅዶች ተዘጋጅተው በሁሉም ተቋማት እየተተገበሩ መሆናቸውን የተገለፀ ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት በኩል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገና በተቋም ውስጥ እያሉ ስለ ስራው ዓለም በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ የስራው ዓለም ገበያ ምን እንደሚመስል እና እንዴት በሰለጠኑበት ሙያ ስራ ማግኘት እንደሚችሉ ግንዛቤ እንዲጨብጡ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የምክር አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እንዲቋቋሙ አቅጣጫ ተቀምጦ በተሰራው ስራ በ22 ዩኒቨርሲቲዎች በተሰጠው ስልጠና እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የምሩቃን የመቀጠር ምጣኔ 60 በመቶ መድረሱን በዳሰሳ መታወቁን የሚኒስትሩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ሪፖርቱን አስመልክቶ የከፍተኛ ትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፈቃድና ከዕውቅና ውጭ በሚሰሩ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተግባር ለመከላከል ሚኒስቴሩ ምን እርምጃዎችን እንደወሰደና ስለመጡ ለውጦች እንዲያብራራ ጥያቄ ከማቅረቡ ባሻገር የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን እንዲያስጠብቁ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባቢነት ኤጀንሲ ሃላፊነቱን እንዲወጣ እየተደረገ ስላለው ድጋፍ ማብራሪያም እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባቢነት ኤጀንሲ የመንግስትንም ሆነ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመከታተልና ለመቆጣጠር አሁን ያለበት ቁመና ከተቋማቱ ብዛት አንፃር የሚያሰራው ሆኖ ባለመገኘቱ የተቋሙን አደረጃጀት በማጥናት በቅርብ ጊዜ የማሻሻያ ሃሳብ ለሚመለከተው አካል እንደሚቀርብ ክቡር ሚኒስትሩ በማረጋገጥ ኤጀንሲው በአደረጃጀት፣ በሰው ሃይልና በሎጅስቲክስ ያለበትን ዕጥረት ተቀብለዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ የተከበሩ አቶ ዋቅጅራ ተርፋሳ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባቢነት ኤጀንሲ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንና ትምህርት ሚኒስቴርንም ጭምር በትምህርት ጥራት ዙሪያ የሚከታተል በመሆኑ ተጠሪነቱ ለሚኒስቴሩ መሆኑ በስራው ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ስላለው ነፃ ሆኖ መስራት የሚያስችለው ቁመና እንዲደራጅ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ኮሚቴው አቋም ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በትምህርት ሴክተር የህዝብ ተሳትፎ ለማሳደግ የህዝብ ክንፍ በመለየት ህዝቡ የትምህርት ጉዳይ ባለቤት እና የችግሩም የመፍትሔ አካል እንዲሆን የተዘረጋውን አሰራር እና በከፍተኛ ትምህርት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በመምህራን ላይና የመምህራን ምጣኔን ለማሳካት የተሰራውን ስራ በጥንካሬ መገምገመን ነው የተከበሩ አቶ ዋቅጅራ ተርፋሳ የጠቆሙት፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በሁሉም ወረዳ አንዳንድ የስልጠና ማዕከላት እንዲኖሩ የተቀመጠው ግብ አሁን ያለው አፈፃፀም ከግማሽ በታች በመሆኑ ግቡን ለማሳካት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ እንዲረባረብ ኮሚቴው ያሳሰበ ሲሆን የመምህራንን አቅም ለማጎልበት ትምህርት ሚኒስቴር ባመቻቸው መርሐ ግብር ተጠቅመው ራሳቸውን ያሻሻሉ መምህራን በከፍተኛ ትምህርት ተቋም በመምህርነት እንዳይቀጠሩ ተደርጎ በመደበኛ ትምህርት መርሐ ግብር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁትን ብቻ በመምህርነት እንዲቀጠሩ የተያዘው አቋም ላይ /የትምህርት ጥራት እንደተጠበቀ ሆኖ/  ማሻሻያዎች በቀጣይ እንዲደረጕም ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ ከህዝብና ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎችም ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡