null Student of selale university said they have facing with the problems of insufficient water and electricity.

በዩኒቨርስቲው ከፍተኛ የውሃ እና የመብራት ችግር በመኖሩ መቸገራቸውን የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሰላሌ ዩኒቨርስቲን ተመልክቷል፡፡

በመስክ ምልከታው ወቅት የተማሪዎች ህብረት ተወካዮች እንዳሉት ዩኒቨርስቲው ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በርካታ ስራዎችን እየሰራ ቢገኝም በቅርቡ ራሱን የቻለ በመሆኑ በርካታ መሰረተ ልማት ስራዎች የሚቀሩት መሆኑን ተናገረው በግቢው ውስጥ የውሃ እና የመብራት ችግር ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ባጋጠማቸው የውሃ እና የመብራት ችግር ሳቢያም በትምህርት ከማሳለፍ ይልቅ ውሃ በመፈለግና መሰል ተግባራትን በማከናወን ጊዜያቸውን በማባከን እየተንገላቱ መሆናቸውንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ገናናው ጎፌ እንደተናገሩት በዩኒቨርስቲው የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተደራጀ መልኩ ለማድረግ በተለይ መሰረታዊ የመማሪያ ቁሶች የሆኑ ቤተ-መጽሐፍትና ቤተ-ሙከራ አገልግሎት ጥሩ የሚባል ቢሆንም በርካታ ስራዎች የሚቀሩት በመሆኑ ለተማሪዎች ክፍት ያልሆኑ አገልግሎቶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም በግቢው ተማሪዎች የሚያነሱት ጥያቄዎች ተገቢ ከመሆናቸውም ባሻገር በዩኒቨርስቲው የሚገነቡ ህንጻዎች ሳይጠናቀቁ የሚዘገዩ በመሆናቸው ምክንያት በቂ የተማሪዎች ማደሪያ የሌለ መሆኑ እንዲሁም አገልግሎት ላይ ያሉ የተገነቡ ህንጻዎችም ጥራታቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው ውሃ የሚያፈሱ መሆናቸውን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በግቢው ያለው ክሊኒክ የተሟላ አገልግሎት ባለመስጠቱ ተማሪዎችን ለወጪ እየዳረጋቸው ከመሆኑም ባሻገር ለድንገተኛ አደጋ የሚያገለግል አምቡላስም እንደሌለና ተማሪዎች  ከአከባቢው ጋር ያላቸው ግንኙነት የላላ በመሆኑ አልፎ አልፎ ግጭቶች ሲነሱ ስጋት ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ ዩኒቨርስቲው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንዳለበት አሳስቧል፡፡      

በዩኒቨርስቲው ለተማሪዎች የመዝናኛ ማዕከልና የሱቅ አገልግሎት አለመኖሩን የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴው ዩኒቨርስቲው ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ለማድረግ አስፈላጊ ነገሮችን ማሟላት ይጠበቅበታል ብሏል፡፡

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው በአዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ተግዳሮቶች በጊዜ ተቀርፈው ለተማሪዎች ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት ካልተፈጠረ ችግሩን አሳሳቢ ሊያደርግ ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው በጥብቅ አሳስቧል፡፡