null The 6 months plan performance report of the Ombudsman institution is low.

የህዝብ  እንባ ጠባቂ ተቋም የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ዝቅተኛ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የተቋሙን የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ተቋሙ በርካታ የአፈጻጸም ጉድለቶች እና የአሰራር ክፍተቶች እንዳሉበት አመላክቷል፡፡

ተቋሙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ከመደገፍ እና ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ከማገዝ አኳያ እንዲሁም የመረጃ ነጻነት አዋጁን አስመልከቶ ግልጽነት ያለው የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ለመፍጠር ከሚደረገው እርብርብ አንጻር ዘርፈ-ብዙ ክፍተቶች እንዳሉበት ቋሚ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሀይሌ በበኩላቸው ቅርንጭፍ ጽህፈት ቤቶችን ለመደገፍ፣ ለመከታተልና ቁጥጥር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ብናደርግም  በአገሪቱ በተወሰኑ ክልሎች የጸጥታ ችግሮች በመኖራቸው ስራዎችን በወቅቱ ማከናወን ሳንችል ቀርተናል ብለዋል፡፡

የመረጃ ልውውጥ ስርዓቱን በተመለከተም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ አንዳንድ  ተቋማት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ የገለጹት ዋና እንባ ጠባቂው በሶማሌ አካባቢ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን አስመልክቶ ባለሙያ ልከው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳት ጥረት ቢደረግም ችግሩን ለመቅረፍ ፖለቲካዊ ውሳኔ እንጂ በእንባ ጠባቂ ተቋም ብቻ የሚፈታ ጉዳይ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራትም በተቋሙ የሰራተኛ ፍልስት፣ ምቹ የስራ ቦታ አለመኖር፣ የተሽከርካሪ እጥረት፣ አስፈጻሚ አካላት ተባባሪ አለመሆን እና ሌሎችም ችግሮች የታዩ  መሆኑን  ዋና እምባ ጠባቂው ተናግረዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ያልተከናወኑ በርካታ ስራዎች በጸጥታ ምክንያት ብቻ እንዳልሆነና ከጸጥታ ጋር የማይገናኙ ስራዎችም አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው በሌላ በኩል የተቋሙ የግማሽ በጀት ዓመት አፈጻፀም ሪፖርቱ የአቀራረብ ብቻ ሳይሆን የይዘት ችግር እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በተቋማት ላይ አስተዳደራዊ በደል ያደረሱ ዜጎች መጋለጥ እንዳለባቸው እና ህጋዊ አርምጃ ለመውሰድ ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው ተቋሙ ለሰራተኞች የተለያዩ ስልጠናዎች መስጠቱን፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የህጻናት ፓርላማ መቋቋሙን እና ለሴት ሰራተኞች የትምህርት አድል መፈቀዱን በጠንካራ አፈፃፀም አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የተቋሙ እቅድና አፈጻጸም ያልተናበበ መሆኑ፣ የተገልጋይ እርካታ በግልፅ አለመቀመጡን፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰጠው ትኩረት ውስንነት እንዳለበት እና የለውጥ ሰራዊት፣ የመልካም አስተዳደርና የመቶ ቀን እቅዶች ተለይተው በሪፖርት አለመቅረባቸውን በክፍተት ገምግመዋል፡፡

በመጨረሻም ዕቅድና አፈጻጸምን አመላካች የሆነ ሪፖርት ካልቀረበ የተሟላ ግብረ-መልስ ለመስጠት ቋሚ ኮሚቴው የሚቸገር መሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸው በቀጣይ ስራዎችን በቅንጅት ለመስራትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁለንተናዊ ርብርብ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡