null The civil society amendment draft proclamation doesn’t give attention to women and the disabled.

የበጎ አድራጎት እና የሙያ ማህበራት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት አልሰጠም ሲሉ የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን በተመለከተ ባካሄደው ይፋ የህዝብ ውይይት ላይ ተሳታፊዎች ገለፁ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን እና የሙያ ማህበራትን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት በፊት የነበረው የሲቪክ ማህበራት አዋጁ አፋኝና ቢሮክራሲው የበዛበት እና ለአሰራርም ዘርፈ-ብዙ እንቅፋቶች እንደነበሩበት ድርጅቶችን ወክለው የመጡ ባለሙያዎችና አመራሮች ተናግረዋል፡፡

የሙያ ማህበራት ተወካዮች እንደገለፁት ረቂቅ አዋጁ ከትርጉም ጀምሮ በተወሰኑት አንቀፆች ላይም የግልጸኝነት ችግሮች እንዳሉበት እና ማህበራት አሁንም የሚጠበቅባቸውን ስራ እንዳይሰሩ የሚገድቡ አመላካቾች እንዳሉበት ጠቁመው አዋጁ ሴቶችን እና ህጻናትን ዋስትናቸውን ያሳጣ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም ተቋሙ ኤጀንሲ መሆኑ ቀርቶ ኮሚሽን መሆን እንዳለበትና ተጠሪነቱም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢሆን የዘርፉን ስራ በብቃት ለማሳለጥ፣ ተጠያቂነትንና ግልጸኝነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ድጋፍና ክትትል ለማድረግ አመቺነት ይኖረዋል የሚል ሀሰብ አንስተዋል፡፡ ማህበራትም ከታክስ ነጻ የሚሆኑበት መንገድ ቢመቻች የተሻለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩልም ማህበራት የአስተዳደራዊና የአላማ ማስፈጸሚያ በጀትን አስመልክቶ በርካታ ችግሮች የነበሩባቸው መሆኑን በውይይቱ የገለጸ ሲሆን አዲሱ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ማህበራት የራሳቸው ገቢ እንዲኖራቸው መፍቀዱ ተቋማት ከጥገኝነት እንዲላቀቁ ከፍተኛ አስተዋፅ አለው ተብሏል፡፡

አዋጁ 20/80 እና 30/70ን በተመለከተም አዳዲስና ገቢ የሌላቸው ድርጅቶችን ታሳቢ ያደረገና ለአገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የበለጠ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡

በውይይቱ የተሳፉ የአካል ጉዳተኞች በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ አካል ጉዳተኞች  ተጠቃሚና አካታች ከማድረግ አንጻር ውስንነት እንዳለበት ገልጸው የምልክት ቋንቋ ትኩረት እየተሰጠው ባለመሆኑ በተለያዩ ስብሳባዎች ሲሳተፉ የትርጉም ሙያተኛ አንደማይኖር ለአብነት አንስተዋል፡፡

በፌዴራል በጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማስረጽ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ በበኩላቸው በማህበራት ስም የሚመጣው የእርዳታ ገንዘብ ለታለመለት አላማ መዋሉን ለማረጋገጥ ክትትልና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው አዋጁ ከትርጉም አንጻር ክፍተቶች ካሉበት እንደገና የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተቋሙን ስያሜና ታክስን በተመለከተ በውይይቱ ወቅት ለተነሱት ጥያቄዎች ዳሬክተሩ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ተቋሙ ኮሚሽን ቢሆን ጥሩ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ተጠሪነቱ ለፓርላማ የሆነ የበጎ አድራጎትም ሆነ የሙያ ማህበር እንደሌለና በተለያዩ አገራት ለተሞክሮ ባደረጉት ፍተሻ አለመገኘቱን አስረድተዋል፡፡ ማህበራትም ከታክስ ነጻ ሊሆኑ እንደማይችሉና ህጉም እንደማይፈቅድም አክለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው ከውይይቱ በርካታ ግብዓቶች እንደተገኙ እና በአዋጁ መካተት ያለባቸው አበይት ነጥቦች እንዳሉ ገልጸው መካትና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ተለይተው አዋጁ በቅርብ ቀን የሚጸድቅ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡