null The House approved members for administrative boundaries and identity issues commission.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላትን ለመሾም የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጸደቀ፣

ምክር ቤቱ ጥር 28/2011 ዓ.ም.ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ስብሰባው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን እና የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽን አባላትን ሹመት መርምሮ አጽድቋል፡፡

በምርጫው የተካተቱት አባላት ከአገሪቱ ከሁሉም ዘርፍ የተውጣጡ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ተዋቂ ሰዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች ናቸው ሲሉ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ጫላ ለሚ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በተመረጡ አባላት ተገቢነት ዙሪያ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት አቶ ጫላ ለሚ እነዚህ ምሁራኖችና ፖለቲከኞች በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ከደር ሆነው ከሚመለከቱ ይልቅ ችግሩን በመለየትና በመፍታት ሂደት ውስጥ ቢሳተፉ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ ብሎ መንግስት ያመነባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ምርጫው አገራችንን ወደፊት ሊያራምድ የሚችል፣ የተደራጀና በጥናት ላይ የተመሰረተ ነገር ለመንግስት ማቅረብ የሚያስችልና አቅም ያላቸው ግለሰቦች ስብስብ እንደሆነም አቶ ጫላ አስገንዝበዋል፡፡

ከተመረጡት 41 የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት መካከል፡­-

 
  1. ዶ/ርሙላቱ ተሾመ
  2. ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ
  3. ዶ/ር ኦባንግ ሜቶ
  4. ዶ/ር ነጋሳ ጊዳዳ
  5. ዶ/ር አረጋዊ በርሄ
  6. ዶ/ር መራራ ጉዲና
  7. አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይገኙበታል፡፡
 

 

እንዲሁም 42 ቁጥር ካላቸው የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽን አባላት መካከል፡­-

 
  1. ዶ/ር ምህረት ደበበ
  2. ኘ/ር በየነ ጴጥሮስ
  3. አርቲስት ደበበ እሸቱ
  4. ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ
  5. ኮ/ል ጐሹ ወልዴ ይገኙበታል፡፡
 

 

ተሿሚዎቹም ከመንግስትና ከህዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሀላ ፈጽመዋል፡፡

ምክር ቤቱም የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ምርጫን በ22 ተቃውሞ በ4 ድምጸ-ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ ሲያጸድቅ የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽን አባላት ምርጫን ደግሞ በ16 ተቃውሞ በ4 ድምጸ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

ምክር ቀደም ሲል የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1101/2011 እና የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1102/2011 መርምሮ ማጽደቁ ይታወሳል፡፡