null The House approves the government definition of powers and duties of the executive organs.

የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻል ማሳየቱን ጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጥቅምት8/2011 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር  ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ በምክር ቤቱ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች በማብራራት የመንግስታቸውን አቋም አስረድተዋል፡፡

በዚሁ ጉባኤ ምክር ቤቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በምክር ቤቱ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት ያደረጉትን ንግግር አስመልክቶ በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ የመንግስትን አቋም አዳምጦ የድጋፍ ሞሽኑን በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል፣

የምግብ  ዋጋ ግሽበት ባለፉት 5 ወራት ከነበረበት 15 በመቶ  በ3 ፐርሰንት በመቀነስ ወደ 12 በመቶ መውረዱን የተናገሩት ክቡር ጠ/ሚ/ሩ በቀጣይም ወደ አንድ አሃዝ ለማውረድ እየተሰራነው ብለዋል፡፡የውጭ ምንዛሬ ክምችትም በ3 ወራት ውስጥ ተቀባይነት ባለው ደረጃ መሻሻሉን አክለው ገልፀዋል፡፡

ደሞዝ ጭማሪን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ ካለው የኑሮ ውድነት አኳያ ጥያቄው ትክክል መሆኑንና ነገር ግን ባለፈው የተጠናው የስራና ደረጃ ምዘና አላማው የደሞዝ ጭማሪ አለመሆኑን አንስተው በአሁኑ ወቅት ባጋጠመን የበጅት ጫና ምክንያት በያዝነው በጀት አመት የደሞዝ ማስተካከያ ለማድረግ አንችልም ብለዋል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ወደ አንድ አሃዝ ሳይወርድ ለሰራተኛው ደሞዝ መጨመሩ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ሃገር አዋጭ እንደማይሆን  አስረድተዋል፡

ለበጀት ጫናውም ከተለያየ ቦታ የተፈናቀሉ ዜጎችን ማቋቋም፣ የገቢ አሰባሰብ ስርዓታችን ደካማ መሆንና የእዳ ጫናዎችን በምክንያትነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ዜጋ ያሉትን የኑሮ ጫናዎች ተቋቁሞ አሁን ያለውን ባለሁለት አሐዝ የግሽበት መጠን ወደ አንድ አሃዝ ለማውረድ መረባረብና እየታየ ያለውን የለውጥ ጭላንጭል ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ በጋራ መቆም ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በአሁን ወቅት አገሪቱን የሚገዳደራት ስርዓት አልበኝነት መሆኑን ያነሱት ጠ/ሚ/ሩ፡ በነሻውም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እና የማይገባቸውን ስልጣን የሚሹ ሃይሎች ፍላጎት  ስራ  ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፤ እናም የህግ የበላይነትን ለማስፈን ህብረተሰቡ  ከመንግስት ጋር እጅ ለእጅ ሆኖ መስራት እንዳለበትና  ለሰላም  ዘብ  እንዲቆም ጥሪ አስተላልፈዋል፡

በአገራች ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ለውጡን በማይደግፉና እንዲቀለበስ በሚፈልጉ ቡድኖች ሴራ ምክንያት የዜጎች ህይወት አልፏል፤ንብረት ውድመት እንዲሁም መፈናቀል አጋጥሟቸዋል፡ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነና ህዝቡም ለጥፋት ኃይሎች በሩን በመዝጋትና አጋልጦ በመስጠት ሊተባበር እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ግጭቶችን ለመፍታት፣ እምቅ የግጭት አከባቢዎችን ለይቶ ፈጥኖ ለማምከን እና ሰለማንና መረጋጋትን  ለማስፈን   መንግስት በአሁን ወቅት በትኩረት እየሰራ  እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ባላት ሃብት ከበርካታ ዓለም አገራት ብትሻልም ነገር ግን እኛ ዜጎቿ ተባብረን ባለበስራታችን ምክንያት በጥቃቅን ችግሮች ኋላቀር አገር ትባላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ እድገታችንን ለማፋጠን የሚያስችል ኢንቨስትመንት መሳብና ዲያስፎራውን ተቀብለን ለማስተናገድ ራሳችንን ማዘጋት አለብን ብለዋል፡፡

ሚዲያ በአንድ አገር ውስጥ የዴሞክራሲ ስርዓትና ባህል ስር እንዲሰድድ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳለው ሁሉ በወጉ ጥቅም ላይ ካልዋለ ደግሞ አጥፊ እንደሆነ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በተለይ ማህበራዊ ሚዲያ አገር ስለሚያተራምስ ትክክለኛ መረጃ ፈጥኖ በመስጠትና ባለመተባበር መመከት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአገሪቱን ሪፎርም ለማስቀጠልና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንበታ የመንግስትም ሆነ ፣ የድርጅትና  የግል የሚዲያዎች  በሃላፊነት ስሜት  ሚናቸውን  እንዲወጡ  ጠ/ሚ/ሩ ጥራቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የድንበር ጥያቄዎችን በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ በተለይም በጎንደርና ሱዳን ድንበር አካባቢ ያለውን ችግር ለመፍታት ከሱዳኑ ፕሬዘዳንት ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነና በውይይት እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡