null The House evaluated 6 months performance report of the Ministry of foreign affairs.

በውጭ ግንኙነት ፖሊሲው የአገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ከማስጠበቅ በተጨማሪ ለአገሪቱ የሚሆን የፋይናንስ ምንጮችን ለመሳብ መሰራት እንዳለበት ተገለፀ፡፡ 

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሔደው 22 መደበኛ ስብሰባው የውጭ ጉዳ ሚኒስቴር የ2011 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የዕቅድ አፋጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል፡፡

ለም/ቤቱ ሪፖርቱን ያቀረቡት ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየው ሚንስቴር መ/ቤቱ በበጀት ዓመቱ አጋሮችን ማፍራትና ወዳጅነትን ማጠናከር፣ በዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ዘንድ የአገሪቱን ገጽታ መገንባት፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራን ማጠናከር፣ የዲያስፖራ ተሳትፎና ጥቅምን ማረጋገጥና ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለአህጉሪቱ ሰላምና ልማት እንዲሁም የኢኮኖሚ ትስስርን በመፍጠር ግንባር ቀደም እንድትሆን የሚያስችል ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ኢኮኖሚ ትስስርን በመፍጠር ከአጎራባች አገራት ጋር የተደረገው ግንኙነት የነበረውን ፈታኝ ሁኔታ የቀየረው በተለይ ከኤርትራ ጋር ለሁለት አስርት አመታት የተቋረጠው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደገና መታደሱንና ወደፊትም በሁሉም ዘርፍ የጠበቀ ትስስርን ለመፍጠር የሚያችል የድንበር ንግድ፣ የወደብ አጠቃቀምና የጉምሩክ ስራ እየተሰራ መሆኑ የሚበረታታ ተግባር እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

በውይይቱም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሪፎርሙን ተቀብሎ ከዚህ በፊት የነበረውን ክፍተት በሰው ሃይል ለመሙላት ባደረገው የሰራተኞች ሽግሽግና ዝውውር የውጭ ፖሊሲን ከግምት በማስገባትና የሰው ሃይል አቅምን ስራ ላይ ለማዋል ታስቦ መሆኑን ም/ቤቱ ደግፎ  የተመደቡ ዲፕሎማቶችም ሆኑ ሚሲዮኖች እውቀትና ብቃት ያላቸው የአገርን ጥቅም ያስቀድማሉ ተብለው የተቀመጡ መሆናቸው በውይይቱ ተነሰቷል፡፡

ም/ቤቱ ከጎረቤት አገራት ጋር ላለው መስተጋብር ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች እየተጠናከሩ ቢገኙም በሱዳን በኩል የሚገቡ የጦር መሳሪያዎች ለአገሪቱ ሰላም ስጋት በመሆናቸው በዚህ በኩል ሚንስቴር መ/ቤቱ ምን እየሰራ እንደሆነ ተጠይቋል፡፡

የጦር መሳሪያዎችን ከሚያመርቱ አገራት ጋር ግንኙነት በማጠናከር ለማስቆምና ሱዳን ላይ ሆነው የሚያዘዋውሩትንም በቁጥጥር ስር የማዋሉን ስራ እየተሰራ እንደሆነ ሚንስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የአገሪቱ ድንበርን በተመለከተ ከኬኒያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና አልፎ አልፎ በሚነሱ ግጭቶችን ለመቅረፍ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ቀጣይ ወደ ስራ የሚገባ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን በኢትዮ-ሱዳን በኩልም ልዩ ኮሚቴ በአዲስ መልኩ ቢደራጅም ከስምምነት ውጭ በድንበር አካባቢ የሰፈሩ የሱዳን ወታደሮችን ሁኔታ መ/ቤቱ ብሔራዊ ጥቅም ሊያስከብር በሚችል መልኩ በጥንቃቄ መመልከት እንዳለበት ም/ቤቱ አሳስቧል፡፡

የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል ትኩረት ተሰጥቶበት የሶስትዮሽ ድርድር ለማስቀጠል ጥናት ተጠንቶ የተለያዩ ምሁራንን ጭምር ዕውቀታቸውንና ጊዜያቸውን በመስጠት ላይ ቢገኙም የታችኛው ተፋሰስ አገራት ስምምነቶችን ባለመፈራረማቸው ሂደቱ እየተጓተተ እንደሆነና በቀጣይም እንዲፈራረሙም ያላሰለሰ ጥረቱን እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም ም/ቤቱ የውጭ ብድርና ዕርዳታን ፍሰትን በማሳደግ የፋይናንስ ምንጮችን በማፈላለግ፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ ለዲያስፖራው ተገቢውን እንክብካቤ እና ባሉበት አገርም መብታቸውና የአካል ደህንነታቸው ተጠብቀው እንዲኖሩ የማድረግ፣ በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር የወጡ ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ አገር ቤት የመመለሱ ስራና ከቋሚ ኮሚቴውና ከም/ቤት አባላት የተነሱ አስተያየቶችንና በእጥረት የተቀመጡትን ችግሮች ለመቅረፍ ሚንስቴር መ/ቤቱ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡