null The House passed to establish identity and administrative boundary commission.

ም/ቤቱ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን በ33 ተቃውሞና በ4 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በአምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ በም/ቤቱ አባላት በርካታ ሃሳቦች ያስተናገደው ይህ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በምክር ቤቱ ዲሞክራሲያዊነት ልቆ እየታየ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ አዋጁን በመደገፍና በመቃወም የተለያዩ ሃሳቦች በስፋት ተንሸራሽረዋል፡፡

አዋጁ በህገ-መንግስቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ለክልሎች የተሰጠውን መብት ይጣረሳል፤ ተግባራቸውን እንዳያከናው ያደርጋል፤ ለህዝቦች የተሰጠውን የማንነት ባለቤትነትን መብት ይከለክላል ከዚህም በተጨማሪ ረቂቅ አዋጁ ህገ-መንግስቱን የሚያሻሽል በመሆኑ ም/ቤቱ ከመወሰኑ በፊት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትና ረቂቅ አዋጁ ቢፀድቅ ቀጥሎ የሚመጣው ውጤት አስከፊ እንዳይሆን የሚል አስተያየት በማቅረብ 3 የም/ቤት አባላት ተቃውመውታል፡፡

በሌላ በኩል ማቋቋሚያ አዋጁን ደግፈው የተከራከሩት የም/ቤት አባላት የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች በዜጎች ዘንድ ለበርካታ ጊዜያት ግጭት ሲያስነሱ የቆዩና በተገቢው መንገድ ምላሽ ሳያገኙ የቆዩ ጉዳዮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ገልጸው አሁን ላይ በአገራችን ጉዳዩ አስከፊ እየሆነ በመምጣቱ በተለይ በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከማንነት ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ ግጭቶች ከ26 ሺህ በላይ የሚደርሱ ዜጎች መፈናቀልና በጫካ ውስጥ ተጠልለው እንዲገኙ መንስዔ መሆኑን አንስተዋል፡፡

መንግስት በህገ-መንግስቱ ለክልሎችም ሆነ ለፌዴሬሽን ም/ቤት የሰጠውን ስልጣን የሚያግዝ እንጂ የሚቃረን እንዳልሆነ በአዋጁ ላይ የተቀመጠ ከመሆኑም ባሻገር ኮሚሽኑ በማንነትና በአስተዳደር ወሰን ጉዳይ ላይ የግጭት መንስዔ የሆኑትን ምክንያቶች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በጥልቀት በማጥናት አማራጭ የመፍትሔ ምክረ ሀሳቦችን ለሚመለከተው አካል ከመስጠት ውጭ በራሱ የመወሰን ስልጣን ያልተሰጠው መሆኑ በአዋጁ ላይ በግልጽ ተደነግጓል በሚል ተከራክረዋል፡፡      

ዛቻ የሚመስሉ የቃላት አጠቃቀሞች የምክር ቤት አባላት የማይመጥኑ መሆናቸውንና  ም/ቤቱም የራሱን መብት ተጠቅሞ ለህዝብ ይበጃል ያለውን አዋጅ እንዳያፀድ እንደማያደርገው አስያየታቸውን የሰጡ የም/ቤት አባል ጠቁመዋል፡፡

ከም/ቤት አባላት በቀረቡት አስተያየቶች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ከህገ-መንግስቱ አንድም አንቀፅ ጋር የማይጋጭ፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለሙዎችና የፌዴሬሽን ም/ቤት አባላት ጋር ውይይት ተደርጎበት ከህገ-መንግስቱ ጋር እንደማይጋጭ የተስማሙበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አክለውም በቅርቡ በሙሉ ድምፅ በም/ቤቱ የአስፈጻሚ አካል ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ከፀደቀው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 ለሰላም ሚንስትር የተሰጠው ተግባር ከህገ-መንግስቱ ጋር እንደማይጋጭ ሁሉ ይህም ረቂቅ አዋጅ ተመሳሳይ ይዘት ያለው በመሆኑ ም/ቤቱ በሙሉ ድምፅ እንዲያፀድቀው ጠይቀዋል፡፡     

በመጨረሻም ም/ቤቱ ሰፊ ክርክሮችን ካስተናገደ በኋላ የማንነት እና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማፅደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በ33 ተቃውሞ በ4 ድምጸ ታቅደቦ በአብላጫ ድምጽ አዋጅ ቁጥር 1101/2011 አድርጎ አጽድቋል፡፡