null Ethiopian National Election Board should timely prevent the challenge facing.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚታዩበት ዘርፈ-ብዙ ችግሮች በአስቸኳይ መቀረፍ እንዳለባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ፓርቲዎቹ በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ያነሱ ሲሆን የበጀትና ፋይናንስ፣ የቢሮና የመሰብሰቢያ አዳራሽ እጥረትን ለአብነት አንስተዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ የማስፈጸም አቅም ውስንነት እንዳለበትና መዋቅሩ እስከታች ድረስ እንደገና መፈተሽ አለበት ብለዋል፡፡  

የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚ አካላት ነጻና ገለልተኛ ሊሆኑ ይገባል ያሉት የተፎካካሪ ፓርቲዎች አሁን ላይ እስከታች ወርደው ከአባሎቻቸው ጋር ለመወያየት ምቹ ሁኔታ እንደሌለ እና በአንዳንድ አካባቢዎች በገዥው ፓርቲ አባሎቻቸው እየተዋከቡና እየታሰሩ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

አክለውም መንግስት ከወሬ ባለፈ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምንም አይነት ድጋፍ እያደረገ እንዳለሆነ፣ ለውጡ መሬት ያልነካ እና ገና ብዙ መስተካከል ያለባቸው አሰራሮች እንዳሉ ለቋሚ ኮሚቴው ጠቁመዋል፡፡      

የቀጣዩን የማሟያ እና አገራዊ ምርጫዎችንም አስመልክቶ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በአንድ ወገን ምርጫ የህዝቦች መፈናቀል፣ መሰደድና መሞት ካልቆመ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ የለም ብለዋል፡፡ ሌላው ወገን ደግሞ ምርጫዎች መካሄድ አለባቸው፤ በህዝብ ያልተመረጠን መንግስት በስልጣን ላይ እንዲቆይ መፍቀድ የለብንም፤  እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ ሁከቶችና ብጥብጦች ሊቆሙ ይችላሉ በማለት ፓርቲያቸውን ወክለው የመጡ አመራሮች ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ምርጫው ይካሄድ ወይስ ይራዘም በሚለው ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎ የህዝቡን ጥቅም ያማከለ ውሣኔ የሚተላለፍ መሆኑን ለፖለቲካ ፓርቲዎች ተናግሯል፡፡

ቦርዱም ያሉበትን ውስብስብ ችግሮች ለመቅረፍ በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኑን እና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ቀጣይ የሚካሄዱው የማሟያም ሆነ አገራዊ ምርጫ ፍትህአዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ የድምጽ መስጫ ሳጥኖችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በተመሳሳይም ቋሚ ኮሚቴው ከቦርዱ ሰራተኞች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ሰራተኞች ከትምህርት እድል፣ ከደመወዝና ጥቅማጥቅም፣ ከአሰራር ግልጸኝነት፣ ከመልካም አስተዳደር እና ከሙስና አንጻር በተቋሙ በርካታ ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል፡፡

በተቋሙ የሰው ሀይል ቅጥር ችግር ያለበትና ዘመድ አዝማድ የበዛበት ከመሆኑ ባለፈ በሙያው የሰለጠነ ብቁ የሰው ሀይል እንደሌለ ገልጸው በሌላ በኩል ተጠሪነታቸው ለማን አንደሆነ በግልጽ ባለመታወቁ የሚገጥሟቸው ችግሮች በወቅቱ እየተፈቱ እንዳልሆነ ነው ቅሬታቸውን የገለጹት፡፡

በተመሳሳም ቋሚ ኮሚቴው ሳሪስ በሚገኘው የምርጫ ቦርድ የሎጀስቲክስና ማሰልጠኛ ማዕከል ባደረገው የመስክ ምልታ እንደተረዳው ተቋሙ በንብረት አያያዝና አወጋገድ ስርዓቱ የተዝረከረከ  ከፍተኛ የሀብት ብክነት የሚታይበት መሆኑን፣ በተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ ክፍተት እንዳለ፣ ግቢው ጽዳት የተነፈገውና የተጎሳቆለ እንደሆነ እና ሰራተኞች በስራ ገበታቸው በሰአቱ እንደማይገኙ ለቦርዱ ለአመራሮች በግልፅ አስረድቷል፡፡

በተቋሙ ሰራተኞች እና በፖለቲካ ባርቲዎች የተነሱት በርካታ ችግሮች በየደርጃው መቀረፍ እንዳለባቸው እና ቦርዱ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ጥረት ማድረግ እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቦ የሪፎርሙን እንቅስቃሴና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን የቅሬታ አፈታት ስርዓት በማድነቅ በቀጣይ ዝርዝር የጽሁፍ ግብረ መልስ እንደሚሰጥ ነው የገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ የቦርዱ አመራሮች በተቋሙ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ገልጸው በቋሚ ኮሚቴው የተነሱ ሀሳቦችን እንደግብዓት ወስደው ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል፡፡