null Northern Wallo Zone could not prevent illegal migration.

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ህገ-ወጥ ስደትን መግታት እንዳልተቻለ ተገለጸ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ባደረገው የመስክ ጉብኝት ህገ-ወጥ ስደትን ለማስቀረት ለወጣቶች የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች የተፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ በምልከታው ተገንዝቧል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉ ተሰሜ ዞኑ ለህ-ገወጥ ስደት ተጋላጭ እንደሆነ ገልፀው ችግሩ ጎልቶ የሚታየው በራያናቆቦ፣ በጎባ ላፍቶ ወልዲያ እንዲሁም በሀብሩና መርሳ አካባቢዎች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ለህገ-ወጥ ስደት መንስኤዎች፣ ወጣቶች ተገቢውን ስልጠና ወስደው በህጋዊ መንገድ እንዳይሄዱ የማሰልጠኛ ተቋማት በቂ አለመሆን፣ ተምሬ ያልፍልኛል የሚል አመለካከት አለመኖር፣ የደላሎች ጉትጎታ፣ በአካባቢው ምቹ የስራ እድል አለመፈጠር እና ሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች መኖራቸውን ወ/ሮ ሙሉ አብራርተዋል፡፡  

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይን ጨምሮ በወረዳ ደረጃ ኮሙኒኬሽን፣ ሴቶችና ህጻናት የአደረጃጀት መዋቅሮች ባለመኖራቸው ስደትን ለማስቆምና ለወጣቶች ምቹ የስራ እድል ለፍጠር በሚደረገው ሁለንተናዊ ርብርብ በርካታ የአሰራር ክፍተቶች ስለሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ አልተቻለምም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል መሬታቸውን ያለአግባብ የተቀሙ በገጠር የሚገኙ ሴቶች የህግ ግንዛቤ ስሌላቸው መክሰስ እንዳልቻሉ፣ ያለ እድሜ ጋብቻና የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ችግሮች እንዳሉ የወረዳው አመራሮች ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም ቋሚ ኮሚቴው በባህር ከተማ አስተዳደር ጉብኝት ባደረገበት ወቅት በገጠር ቀበሌዎች የሚገኙ 33 ሴቶች መሬታቸውን ያላአግባብ እንደተቀሙ እና ለከፍተኛ የፍትህ እንግልት መዳረጋቸውን፣ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ አደንዛዥ እፆች በመበራክታቸው ትውልዱ ለደባል ሱስ እየተጋለጠ መሆኑን መረዳት ችሏል፡፡

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ አምሳል ካሳው በ2011 ዓ.ም በአምስት ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር ወንጀል የተፈጸመ ሲሆን ጥቃት ባደረሱ ግለሰቦች ላይ መንግስት በተወሰኑት እርምጃ መውስዱን እና በቀሩት ላይም ክስ ተመስርቶባቸው ለህግ እንዲቀርቡ በሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በስራ እድል ፈጠራ ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ዘርፈ-ብዙ ችግሮች እንዳሉ የጠቆሙት ወ/ሮ አምሳል ተደራጅተው ለመስራት የተዘጋጁ ወጣቶች ብድር ለማግኘት ቢሮክራሲው እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም በባህርዳር ከተማ በበጀት እጥረት ምክንያት የህጻናት ማቆያ ግንባታዎች  አለመጀመራቸውን፣ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ወደጎዳና ህይወት የሚቀላቀሉ ህጻናት በከተማዋ እንደሚታዩ እና የህጻናት የጉልበት ብዝባ ችግሮችም እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የክልሉ አመራሮችን አግኝቶ የሴቶችን ተጠቃሚነት እና የአመራር ሰጭነት ለማጎልበት፣ የሚደርስባቸውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል በየደረጃው ዘርፈ-ብዙ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡