null Trade Competition and Consumers Authority to introduce digital system to control defects in k.g.

ሸማቹን ማህበረሰብ የሚጎዱ የኪሎ መቀነስ የሚይባቸውን የክብደት መለኪያ ሚዛኖች ወደ ዲጂታል የመቀየሩን ስርአት ተግባራዊ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡  

ቋሚ ኮሚቴው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋጋን ከማረጋጋት አንጻር ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዲሰፍን እየሰራ ያለ ቢሆንም በነጋዴው ማህበረሰብ ውስጥ ውድድርን በሚያዛባ መልኩ ዋጋን ተመሳጥሮ የመጨመሩ ሂደት እየተባባሰ እንደሄደ በሸማቹ እየተገለጸ በመሆኑ ለችግሩ መፍትሄ ከማምጣትና አስተማሪ እርምጃ ከመውሰድ ረገድ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁሟል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በበኩሉ በክልሎች ያጋጠሙ የአፈጻጸም ችግሮችን ለማሻሻል በአዋጅ ቁጥር 813/2006 ያሉ ደንብና መመሪያዎችን ለማሻሻል አዋጁን በመፈተሸና ተሞክሮን በመቀመር የጋራ ውይይት ማድረጉን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ተክሉ እንደገለጹት ሚዛንን በሚመለከት ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሳምፕል ሚዛኖችን በመውሰድ ማስጠናታቸውን ገልጸው ከስጋ ቤቶች በተወሰደው ሳምፕል ከ135 እስከ 139 ግራም እንደሚጭበረበርና በተመሳሳይም ሌሎች ምርቶች ላይም ችግሮች እንደታዩ በጥናት መታወቁን ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ህብረተሰቡ በህጋዊ ሚዛን እንዲመዘንልኝ ብሎ መብቱን እንዲያስጠብቅና እንዲንቀሳቀስ በማስተማር እና ጥናት በማስጠናት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ዲጂታላይዝድ ሚዛን የሚገባበት ስርአት እንዲመቻች ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምርጥ ተሞክሮዎችን  በማጥናትና በመቅሰም በንግድ ስርአቱ ላይ ፍትሃዊ የውሳኔ አሰጣጥ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለማረጋጋት ያለው ክትትልና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴው ሰብባቢ ወ/ሮ አማረች ጣሰው አሳስበዋል፡፡